የውሃ ልማት ፈንድ ጽ/ቤት ከውሃ ሀብት አስተዳደር ፖሊሲና ስትራቴጂ መርሆዎች አንዱ የሆነውን ዋጋ የማስመለስ መርሆ መሰረት በማድረግ ከውጭ ብድርና ዕርዳታ ሰጪ መንግስታትና ተቋማት ፈንድ በማሰባሰብ ለአገራችን ከተሞች የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን መሰረተ ልማቶች ማስፋፊያና ለመስኖ ልማት ፕሮጀክቶች ማስፈፀሚያ የረዥም ጊዜ ብድር የማቅረብ ዓላማን አንግቦ በጥር ወር 2004 ዓ.ም በአዋጅ ቁጥር 268/1994 የተቋቋመ መንግስታዊ ተቋም ነው፡፡
የፈንዱ ዋና ዓላማ ከፍ ብሎ በተጠቀሰው መንገድ የሚያስተላልፋቸውን ብድሮች በስምምነቱ የጊዜ ማዕቀፍ ውስጥ መልሶ በመሰብሰብ ለሌሎች ተመሳሳይ የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን መሰረተ ልማት ጥያቄ ለሚያቀርቡ ከተሞች ፕሮጀችክቶች ማስፈፀሚያ የሚውል ተዘዋዋሪ ፈንድ ክምችት መፍጠርና ማስተዳደር ነው፡፡
ጽ/ቤቱ ሥራውን በይፋ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በ106 ከተሞች ለሚገኙ 114 ፕሮጀክቶች ብድር የሰጠ ሲሆን የተሰጠው የብድር መጠንም(ስምምነት የተፈራረምናቸዉን አካቶ) 9.8 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ከነዚህ ፕሮጀክቶች መካከልም በአሁኑ ወቅት 34 የሚሆኑቱ ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል፡፡ ከነዚህም ውስጥ 17ቱ ከተሞች ብድራቸውን መመለስ የጀመሩ ሲሆን 17ቱ ደግሞ ብድሩን ለመመለስ በዝግጅት ላይ ይገኛሉ፡፡
በ2007 ዓ.ም ማለትም በ2ኛዉ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዘመን ጽ/ቤቱ ከሚሰጠዉ የብድር ተጠቃሚ የሆኑት የውሃ አገልግሎት ድርጅቶች ስምምነት የተፈረመባቸዉና ሥራ ያልተጀመረባቸዉ 15 የዋን ዋሽ ከተሞችን ጨምሮ በቁጥር 51 እንደነበሩ የሚታወስ ነዉ፡፡ ሆኖም ጽ/ቤቱ ባወጣዉ ዕቅድ በ2012 መጨረሻ የመጠጥ ዉሃ ፕሮጀክቶችን ቁጥር ወደ 106 ለማሳደግ ዕቅድ ይዞ ሲሰራ የቆየ ቢሆንም ገና 18 ወራት እየቀሩ ከዕቅድ በላይ 114 ፕሮጀክቶችን ፋይናንስ ማድረግ ተችሏል፡፡ ይህ አፈጻጸም የሚያመለክተዉ በተሻሻለው ስታንዳርድ መሰረት በአገር አቀፍ ደረጃ የከተሞችን የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን አገልግሎት ሽፋን 75 በመቶ ለማድረስ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት የዉሃ ልማት ፈንድ የበኩሉን እየተወጣ እንደሆነ ነዉ፡፡
በሌላ በኩል ከዚሁ ፈንድ በቀረበላቸዉ ብድር ህዝቦቻቸዉን ተጠቃሚ አድርገዉ ከነበሩባቸዉ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች በመላቀቅ ዛሬ ትልቅ ላይ ደረጃ ደርሰዉ የዉሃ ልማት ፈንድን ታላቅ ባለውለታነት እየመሰከሩ የወሰዱትንም ብድር በወቅቱ እየመለሱ የሚገኙ ከተሞች ያሉትን ያህል ጥቂት ከተሞች በተለያዩ አስተዳደራዊ ችግሮች ምክንያት የወሰዱትን ብድር በምንጠብቀዉ መጠንና ጊዜ ያለመመለስ ሁኔታዎች ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል፡፡ ይህ የሚቀጥል ከሆነ የዕድሉ ተጠቃሚ ለመሆን በጉጉት የሚጠባበቁቱ በርካታ ብድር ፈላጊ ከተሞች የፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ ለማንሳት የሚገደዱበት ሁኔታ የሚፈጠር ከመሆኑም ሌላ ፈንዱም ማደግ በሚገባዉ ልክ ሊያድግ ስለማይችል ዓላማውን ለማሳካት ከመቸገሩም በላይ፤ በመንግስት ላይም የመልካም አሰተዳደር ጥያቄ ማስነሳቱ የማይቀር ነዉ፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የተበደሩትን ገንዘብ በሰላማዊ መንገድ መመለስ ሳይቻል ሲቀር ወደ ፍርድ ቤት መኬዱ ስለማይቀር ሰላማዊና መተሳሰብ የሰፈነበትን ግንኙነታችንን ከመጉዳቱም በላይ የተበዳሪ ከተሞችንም ሆነ ለብድሩ ዋስትና የሰጡትን ክልሎች መልካም ስምና ዝና የሚያጎድፍ ታሪክ ሆኖ ይመዘገባል፡፡
በመሆኑም ከነዚህና ከመሰል ችግሮች ለመዳንና ፈንዱ ከተቋቋመበት ዓላማ አንጻር አስቀድሞ የሰጠዉን ብድር በወቅቱ እየሰበሰበ ለሌሎች ተራዉ ላልደረሳቸዉ ከተሞች ተደራሽ እየሆነ በከተሞቻችን የሚስተዋለዉን ከፍተኛ የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ችግር ለማቃለል ብሎም በረዥም ጊዜ የውሃዉ ዘርፍ ከውጭ ብድርና ዕርዳታ ጥገኝነት እንዲላቀቅ የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ እንዲቻል ከዉሃ ልማት ፈንድ ብድር ተጠቃሚ የሆኑ ከተሞች የብድሩን መልሶ መክፈያ ጊዜ ጠብቀው የሚፈለግባቸውን የብድር ተመላሽ ለፈንዱ በወቅቱ ገቢ ማድረግ አንደሚኖርባቸውና ዋስትና የሰጡ የክልል መንግስታትና የየከተሞቹ አስተዳደሮችም ለዚሁ ጉዳይ ልዩ ትኩረት በመስጠት የዉሃ አገልግሎት ድርጅቶቹን በባለቤትነት መንፈስ ሊደግፉና ሊከታተሉ እንደሚገባ ለማሳሰብ እወዳለሁ፡፡
የውሃ ልማት ፈንድ የሚያቀርበው ብድር በቂ የእፎይታ ጊዜ ያለውና ከ20 እስከ 30 ዓመት ጊዜ ውስጥ እጅግ አነስተኛ ከሆነ ወለድ (3%) ጋር ተመልሶ የሚከፈል ከትርፍ ይልቅ ልማቱ ላይ የሚያተኩር ሲሆን የአገራችንን ከተሞች የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ችግር በተቻለ ፍጥነት በመፍታት ከተሞቻችን በኢኮኖሚውም ሆነ በማህበራዊ እንቅስቃሴዎቻቸው ተወዳዳሪና ተፎካካሪ ሆነው ለነዋሪዎቻቸዉ ምቹ የመኖሪያ ሥፍራዎች እንዲሆኑ የሚተጋ ተቋም በመሆኑ ከፈደራል እስከ ከተሞች ድረስ የሚገኙ ሁሉም ባለድርሻዎቻችን ይህ ቅዱስ ዓላማ የተሳካ እንዲሆን አብረውን እንዲሰሩ እጠይቃለሁ፡፡
በመጨረሻም የብድር ፋይናንሱ ምንጭ ከሆኑ የልማት አጋሮቻችን መካከልም የአለም ባንክ፣ የአውሮፓ ኢንቨስትመንት ባንክ፣ የአፍሪካ ልማት ባንክ፣ የፈረንሳይ ፣ የጣሊያንና የእንግሊዝ መንግስታት በግምባር ቀደምትነት ሊጠቀሱ የሚገባቸው በመሆኑ በራሴና በውሃ ልማት ፈንድ ስም ምስጋናዬን እያቀረብኩ ወደ ፊትም የተለመደ የአጋርነት ትብብራቸዉን አጠናክረዉ እንዲቀጥሉ እና ሌሎችም የእነርሱን አርአያ በመከተል የልማት አጋርነታቸውን እንዲያረጋግጡ ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡
አመሰግናለሁ።